አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2009 የኢትዮጵያ ሥነ – መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የዶክትሬት ዲግሪና ሁለት የድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ትምህርት ቤቱ ዛሬ በመደበኛ መርሃ ግብር በአምስት የተለያዩ የሥነ – መለኮት ዘርፎች ያስተማራቸውን 61 ተማሪዎች አስመርቋል ፤ ከዚህ መካከልም 12ቱ ሴቶች ናቸው።
የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ዶክተር ምስጋና ማቴዎስ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ትምህርት ቤቱ በመጪው ዓመት ‘ፕራክቲካል- ቲዎሎጂ’ና ‘ፐብሊክ -ቲዎሎጂ’ የሚባሉ የድኀረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ይጀምራል።
ከሁለቱ መርሃ- ግብሮች በተጨማሪ ከፍሪ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ አምስተርዳም ጋር በመተባበር የዶክትሬት ዲግሪ እንደሚጀመር ገልጸው፤ የእነዚህ መርሃ ግብሮች መጀመር የትምህርት ቤቱን የቅበላ አቅም ከ200 ተማሪ በላይ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቱ ያስተማራቸው ሠልጣኞች ማህበረሰቡንና ቤተክርስቲያኗን እንዲያገለግሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ተመራቂ ተማሪዎች በተማሩበት ዘርፍ በትህትና የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ተመራቂ ተማሪዎቹ በሙያቸው ባገኙት እውቀት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡና ማህበረሰቡንና ቤተክርስቲያንን እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሥነ-መለኮት ድኀረ ምረቃ ትምህርት ቤት ከተመሰረተ ጊዜ አንሰቶ 526 ተማሪዎችን አስመርቋል።
በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቱ በአዲስ አበባና ሆለታ ከተሞች ላይ ለእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ድጋፍ እያደረገ መሆኑም ተወስቷል፡፡
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብም የ100 ሺ ብር ቦንድ ግዢ መፈፀሙ ተገልጿል።
ትምህርት ቤቱ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ የሱስ፣ በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያንና በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከ20 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ነው።